ሊነበብ የሚገባ- የጃዋር ንግግር በሚንያፖሊስ በጥንቃቄ የተተረጎመ
የጃዋር ንግግር በሚንያፖሊስ (መስከረም 23, 2009/ ኦክቶበር 3, 2016 ያደረገዉ)
===================================================
ቅድመ ንባብ ማስታወሻ:-
ይሄን የጀዋርን ንግግር በጥንቃቄ ተርጉመዉ ያደረሱን ለአንዲት ኢትዮጵያ ህልዉና የታመነ ልብ እና የጸና አላማ ያላቸዉ ብሎም ዲሞክራሲያዊት ኢትዮጵያ እንጅ መፈጠር ያለባት የኢትዮጵያ ህዝብ መከፋፈል የለበትም ብለዉ በታላቅ ሀገራዊ ተጋድሎ ዉስጥ ያሉ የኦሮሞ ልጆች ናቸዉ::መጀመሪያ እነሱን በኢትዮጵያ ህዝብ ስም አመሰግናለሁ::ቀጥሉም ሁሉም ኢትዮጵያዊ ይሄን የጀዋርን ንግግር እንዲያነበዉ እጋብዛለሁ::መልካም ንባብ !
=================================
ለጊዜዉ ሁላችንም ስሜታዊ ነን። መለስ ብለን ስናይ በውጭ ሃገር መሰራት የሚገባቸው ሁለት ነገሮች አሉ። አንዱ የፖለቲካ ማህበረሰባችን ማለትም በየደረጃው ያሉ የፖለቲካ መሪዎቻችንና፡ ምሁሮቻችን ሊሰባሰቡ፥ ሊደማመጡና መግባባት ላይ ሊደርሱ ይገባቸዋል። ቀጥሎ ሃገር ቤት በመደረግ ላይ ላለው ትግል በየዘርፉ ድጋፍ ማደረግ ያስፈልጋል። ስራ እየተሰራ ነው። ይሄ ስራ ተጠናክሮ መቀጠል አለበት።
አንድ የፖለቲካ መሪዎቻችንን የመሸምገልና የማቀራረብ ስራ ሙሉ በሙሉ ባይሳካም ጅማሮው በራሱ አንድ ነገር ነውና ተጠናክሮ መቀጠል አለበት። ነገር ግን ከፊት ለፊቴ ቁጭ ያላችሁ መሪዎች ቀልዱን አቁሙ:: ካሁን ብኋላ ቀልዱን ልናስተናግድ አንችልም። ወያኔ ሕዝባችንን ገድላ፥ ይቅርታ ጠይቃን : ለቅሶ ቁጭ ብለዉልን እየቀለዱብን ነው። እናንተም ሕዝባችንን አንድ እናደርጋለን እያላችሁ እየለያያችሁ ነው። ይሄን ቀልድ ከእንግድህ የምንቀበለዉ አይደለም። ቀልዱን አቁሙ።
በሙሁሮቻችን በኩል ስራዎቻችንን በሶስት ደረጃ ከፍለን እየሰራን ነው። አንደኛ ይሄ መንግስት ሊወድቅ ነውና የሽግግር መርሃ ግብር ሊኖረን ይገባል። በዚህ ረገድ አለማቀፍ የኦሮሞ ሕግ ባለሙያዎች ማህበር እየሰራበት ነው፥ የተለያዩ ሰነዶችን እያዘጋጁ ነው። በዚህ ወር መጨረሻ በ23 ይመስለኛል ለንደን ላይ ኮንፈሬንስ ይኖረናል። እኛ ሁላችንም እንሳተፋላን:: አብረን እንሄዳለን ማለት ነው።
የሽግግሩ ሰነድ ኦሮሚያ በሽግግሩ ወቅት ምን መምሰል አለባት፥ ምን አይነት መንግስት መገንባት ትፈልጋለች፥ ምን አይነት ግንኙንት ሊኖራት ይገባል የሚለውን ሁሉ ይመልሳል:: ሁለተኛው በውጭ ሃገር የሚገኘው ማህበረሰብ አመራር ማለትም አመራር ስንል የማህበር፥ የዕምነት፡ እና የተለያዩ ተቋማት ፖለትካል እና ሲቪክ ሶሳይት መሃክል መግባባት መፍጠር ነዉ::
ሁለተኛ ትልቁን ችግራችንን ልንገራችሁ። የሚሞቱትን መቼም ባብዛኛው ከእናንተ እኔው ነኝ ቀድሜ የምሰማውና በጣም ዘግናኝ ነው። መሞታቸው ብቻ አይደለም የሚያሳዝነዉ:: የሚሞቱትን መርዳት አለመቻላችን ያሳዝናል:: ለመርዳት አቅም ማጣታችን ብቻ አይደለም እንዳንረዳቸዉ ያደረገን:: ለመርዳት የሚሆን ሀብ ኖሮንም መርዳት አልቻልንም:: ሰው በየቀኑ እየደወለልኝ “ገንዘበን መስጠት እፈልጋለሁ፥ መኪናየን፥ ቤቴን ሽጨ መርዳት እፈልጋለሁ እንዴት ልሪዳ ብሎ ይጠይቁኛል።” እኔም አላቅም ብየ እመልሳለሁ። ምክንያቱም ይሄንን የሚተገብር ተቋም የለንም። አንዳንድ ነገር እዚያም እዚያም ብየ ትንንሽ ነገር አደረጋለሁ። ይሄ ግን የተበታተነ ስለሆነ አንድ በናሽናል ደረጃ የተማከለ ነገር ያስፈልጋል:: የኦሮሞ እርዳታ ማህበር (Oromo Relief Assocciation) ያስፈልገናል።
ሌላዉ የዲፕሎማሲው ስራ ለጉድ እየተሰራ ነው። እንክሪደብል (Incredible)! እኛንና አበሾቹን አነጻጽራችሁ ብታዩ፥ እነሱ እንደ ኤሊ እየተንፏቀቁ ነው። እኛ ደግሞ እንደ ድኩላ ፈጥነን እየሮጥን ነው። በዚህ ልትኩራሩበት ይገባል። በመሪዎቻችሁ ልትኩራሩ ይገባል። በታሪካችን ውስጥ ለመጀመሪያ ግዜ የዓለም መሪዎች እያዳመጡን ነው።
በተጨማሪም ወታደራዊና ደህንነት ተቋማትን፥ ሕግ አውጭዎችን፥ ሰብዊ መብት ተቋማትን የምናገኝበት መንገድ በደንብ እየተከፈተ ነው። ይሄ ጥሩ ነው፡ ግን በቂ አይደላም። ለምን? ግራ እጅ የሚሰራውን ቀኝ እጅ ካላገዘ፡ የዲሎማስ ስራችንን ካላስተባበርን፡ የዲያስፖራውን እንቅስቃሴ ካላስተባበርን፡ ስራ በአዉሮፓ እና በአዉስትራሊያ ሆነው ለሚሰሩ ሀይሎች በቂ ገንዘብ ካልተመደበ እና አሰራሩ ካልተማከለ (Centralized) ዉጤታማ መሆን አንችልም::
በለንደን ከሚዘጋጀው የሽግግር ሰነድ ቀጥሎ በአትላንታ ጆርጂያ የተጋድሎአችን አንደኛ ዓመት ላይ የኦሮሞ መሪዎች ጉባኤ ( Oromo Leadership Conference) ይኖረናል። በዚህም የፖለቲካ፥ የማህበራዊና እምነት ተቋማት መሪዎቻችን በሙሉ ይሳተፋሉ::በዚህ ጉባኤ ላይ መሰረታዊ የኦሮሞ ነጻነት ቻርተር (Oromo Basic Freedom Charter) እና ለዲፕሎማሲ ስራ እና ግብረሰናይ ተቋማት ለማግኘት መርህ የእስትራቴጂ ሰነድ ይዘጋጃል። ይሄ በተጨባጭ እየተሰራ ነው:፡ እየሰራን ነው። እኛም የምንሳተፈው በዶ/ር አሰፋ ጃላታ መሪነት ዓለማቀፍ መልክ ያለው ሁሉንም የኦሮሞ ፖለቲካ መሪዎቻችንንና ተቋማትን ያቀፈ ተቋም ዕውን እንዲሆን ነዉ:: እየሰራን ነው። ዋናዉ ችግራችን ግን መሬት ላይ ያለው ተጨባጭ ሁኔታ በጣም በፍጥነት እየሄደ ነው። እኛ ግን መድረስ እያቃተን ነው። እናም በፍጥነት መጓዝ ያስፈልጋል።
እየኮረኮረቻችሁ ያለች እኔ እስካሁን ያልተናገርኳት አንድ ነጥብ አለች። እስካሁን የሰራናቸው ስራዎች በሙሉ ነገ ኦሮሚያን የምናበጅባት ማለትም የኦሮሞ ነጻነት ትግል ማለት ነው። ልክ ቤት ያለ ምሰሶ መቆም እንደማይችል፥ የሰው ልጂ ያለ አጥንት መንቀሳቀስ እንደማይችል፥ የምንሰራቸው ስራዎች ዲፕሎማስ በል፡ የመገናኛ ብዙሃን ስራ በል፡ የምሁራን ስራ በል ያለ ወታደራዊ ሐይል ወደፊት ሊጓዙ አይችሉም:: ወያኔን ጫፍ ላይ አድርሰናታል። ከፍተኛ መስዋዕትነት እየከፈልን ነው። እስከ መቼ እንሞታለን? መግደል ነው እንጂ! ግን ሞትን ድል ነስተናል:: ይሄን እንዳትርሱ። ንዴትና በቀላችንን መወጣት ቢያቅተንም በስልታዊ አካሄድ ብዙ ድሎችን አግኝተናል። ይሄ ስርዓት የዛሬ አስር ዓመት ካለበት የለም። በርግጥ ዛሬ የትናንቱ ቦታ ላይ አይደሉም። አዳክመናል ከመሬት ማድረስ እንችላለን።
ሁላችሁም መርሳት የሌለባችሁ የኦሮሞ ሕዝብ ትግል ወያኔን ለመጣል አልተጀመረም፡: የኦሮሞ ሕዝብ ትግል የነፍጠኛውን ስርዓት ለመጣል አልተጀመረም:: የኦሮሞ ሕዝብ ትግል ማንኛውንም ዓይነት አፋኝ ስርዓት ገርስሶ የበለጸገች ከራሷና ከሕዝቧ ጋር የታረቀች፥ ሰላም ሰፍኖባት መታረዝ፡ ሞትና ስደት የሌለባት ኦሮሚያን መገንባት ነው ግቡ።
ይሄን ለማድረግ የዲፕሎማስ እና የብዙሃን መገናኛ ስራ አስፈላጊ ነዉ:: እንዲሁም በመሃከላችን መከባበር ብሎም በዉጭም እራሳችንን ማስከበር ወሳኝ ነዉ:: ለዚህም በደንብ የታጠቀና የተደራጀ ወታደራዊ ኃይል ያስፈልገናል። ይሄኛውን ጉዳይ እንደ ሌሎቹ ፍርጥርጥ አርጌ ማውራት አልፈልግም።
ለአንድ ነገር ግን ራሳችሁን ማዘጋጀት አለባችሁ። የሕዝባችን ትግል መቀጠል አለበት። ተቋሟዊ እና ስልታዊ በሆነ መንገድ ሕዝባችን ራሱን የመከላከል አቅም እያጎለበት መሳሪያ እየነጠቀ እጁ እያስገባ፡ እራሱን እያደራጀ ሄዶ የራሱን የኦሮሚያ መከላከያ ሰራዊት መገንባት ይጠበቅብናል።
ይህ በአንጃባ አይሆንም። ይሄ ሁለት ነገር ይጠይቃል። ሃገር ውስጥም ውጭ ሃገርም ያለው አቅም ያለው ወጣታችን ወደ ትጥቅ ትግል መሄድን ይጠይቃል። ጀዋር ሴንተራል አቬኑ ውስጥ ቁጭ ብሎ ሰራዊት መገንባትና መምራት አይችልም። ወታደር በሁለት ምክንያት ይዋጋል። አንድ አዛዡን ስለሚፈራ። ሁለት በአዛዡ ስለሚመካ። ስለዚህ በደንብ እናስብበት።
በኦሮሚያ ውስጥ ወደ አምስት መቶሽ የጦር መሳሪያ አለ። ይሄ ሁሉ የኛ ነው፡: በልጆቻችን እጅ ነው ያለው። ሆኖም ግን አንድ ችግር ልንገራችሁ። ይሄ የወያኔ ወታደር ከድቶ መውጣት አቅቶት ይመስላቿሃል? በየቀኑ ከጀነራል እስከ አስርአለቃ ያገኙኛል። እዛው ሁኑ ነዉ የምላቸው። የት ነው የምወስዳቸው ታዲያ? ወጥው እንዲያልቁ ማዘዝ አለብኝ? አላስፈላጊ መስዋዕትነት ማስከፈል ተገቢ አይደለም። ከኋላ ወያኔ ከፊት ለፊት የኦሮሞ ወጣቶች ግድ ሆኖባቸው የሚችሉትን ወጣቱን እየገደሉ ነው። እናም ይሄ ሀይል መጠለያ አግኝቶ ተመልሶ ስርዓቱን የሚዋጉበት ነገር ላይ መሰራት አለበት። ይሄን ለማዘጋጀት ለሚያስፈልጉት ቁሳቁስና ገንዘብ ልትዘጋጁ ይገባል።