ባህር ዳር መጋቢት 29/2008 የባህር ዳር ዩኒቨርስቲ ከሚቀጥለው ዓመት ጀምሮ የግዕዝ ቋንቋ ትምህርት ለመጀመር የሚያስችለውን ዝግጅት እያደረገ መሆኑን አስታወቀ፡፡
ሀገር አቀፍ የግዕዝ ቋንቋ አውደ ጥናት በባህር ዳር ዩኒቨርስቲ አዘጋጅነት በመካሄድ ላይ ነው፡፡
የዩኒቨርስቲው ፕሬዚዳንት ዶክተር ባይሌ ዳምጤ በአውደ ጥናቱ ላይ እንደገለፁት በዩኒቨርስቲው የግዕዝ ትምህርት እንደ አንድ የትምህርት አይነት እንዲሰጥ ዝግጅት እየተደረገ ነው።
ትምህርቱን በሚቀጥለው ዓመት በመጀመሪያና በሁለተኛ ዲግሪ ለመጀመር ጥናት ተካሒዶ የስርዓተ ትምህርት ቀረፃ መጀመሩን ገልፀዋል።
ዩኒቨርስቲው የአጭር፣ የመካከለኛና የረጅም ጊዜ ስልጠናዎችን እየሰጠ ከመሆኑም በላይ በግዕዝ ቋንቋ የተፃፉ ጽሁፎችን በመሰብሰብ አደራጅቶ ለመጭው ትውልድ ለማስተላለፍ የሚያስችሉ ስራዎችን እያከናወነ እንደሚገኝም ገልፀዋል፡፡
በዩኒቨርስቲዎች እየተሰጠ ያለው ትምህርት የምዕራባውያን ቅኝት ነው ያሉት ዶክተር ባይሌ የትምህርቱ መጀመር ዜጎችን በሃገራዊ እውቀት፣ ክህሎትና አመለካከት ለመቅረጽ የሚደረገውን ጥረት ያግዛል ብለዋል፡፡
ቋንቋውን ወደ ነበረበት በመመለስ ቀደም ሲል ተጽፈው የተቀመጡና ለመድሃኒት ቅመማ፣ ለህክምና፣ ለምርምርና ሌሎች አገልግሎቶች የሚውሉ እውቀቶች ጥቅም ላይ እንዲውሉ መደረግ እንዳለበት አስረድተዋል።
የአውደ ጥናቱ ዓላማም ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ተቀራርቦ በመነጋገር ቋንቋውን ለማሳደግ ዘላቂነት ያለው መፍትሄ ለማስቀመጥ የሚያግዝ እንደሆነም ጠቁመዋል።
በአማራ ክልል የሚገኙ የመንግስት ዩኒቨርስቲዎች አማካሪ አቶ ይትባረክ ደምለው በበኩላቸው ግዕዝ በኢትዮጵያ ታሪክ በትምህርት፣በማህበራዊ ፣ በኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ እንቅስቃሴዎች የጎላ ሚና እንደነበረው ገልጸዋል።
በዚህም የሃገሪቱን ቀደምት ስልጣኔ፣ ታሪክ፣ ባህልና ብልፅግና ለአሁኑ ትውልድ እንዲተላለፍ በማድረግ ቋንቋው ባለውለታ እንደሆነም ተናግረዋል።
ቋንቋው በአሁኑ ጊዜ ከብሄራዊ መግባቢያነት ወደ ቤተክርስቲያን መገልገያነት እየተቀየረ በመምጣቱና በመደበኛ ትምህርት ቤቶችም ስለማይሰጥ የመጥፋት አደጋ እንዳይገጥመው በትኩረት ሊሰራ እንደሚገባው ተናግረዋል።
ቋንቋው ታሪካዊነቱን እንደጠበቀ ለመግባቢያ፣ ለምርምርና ለኪነ ጥበባዊ አገልግሎት እንዲውል ዩኒቨርስቲዎች የጀመሩት ጥረት ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት አሳስበዋል፡፡
በባህር ዳር ስላሴ ካቴድራል የቅኔና የመጸሐፍ ቅዱስ መምህር ቅዱስ ያሬድ በበኩላቸው የግዕዝ ቋንቋ በቤተክርስቲያን ሰፊውን አገልግሎት እየሰጠ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
ዩኒቨርስቲው ቋንቋውን ለማሳደግ የጀመረው ጥረት የሚያስመሰግነው መሆኑን አመልክተዋል።
የግዕዝ ቋንቋን ወደ ተሻለ ደረጃ በማሳደግ ለማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ መስተጋብሮች ጥቅም ላይ እንዲውል ዩኒቨርስቲዎች፣ አብያተ ክርስቲያናትና የሚመለከታቸው አካላት ተቀናጅተው መስራት እንዳለባቸው አስታውቀዋል፡፡
ባህር ዳር ዩኒቨርስቲ ለሁለት ቀናት ባዘጋጀው የግዕዝ ቋንቋ አውደ ጥናት ላይ አዲስ አበባን ጨምሮ በአማራ ክልል የሚገኙ ዩኒቨርስቲዎች ተወካዮች፣ ምሁራን፣ የሃይማኖት አባቶችና ተመራማሪዎች ተሳታፊ ሲሆኑ የተለያዩ ጥናቶች ቀርበው ውይይት እየተካሄደባቸው ነው፡፡