ፌስቡክ በህይወታችን ውስጥ ምን ያህል ተፅዕኖ እያሳረፈ ነው?

የወቅቱ ዋነኛ የመረጃ መቀባበያ እየሆነ የመጣው ግዙፉ የማህበራዊ ትስስር ገጽ ፌስቡክ ከበርካታ ጥቅሞቹ ባሻገር ከአጠቃቀም ጉድለት የተነሳ አካላዊ እና አዕምሯዊ ጉዳቶቹም እየጎሉ መጥተዋል።

ለበርካታ ስአታት ፌስቡክ መጠቀም እንቅልፍ ከማሳጣት ባለፈ የማህበራዊ ግንኙነታችን እየሸረሸረ ነው የሚሉም በርካቶች ናቸው።

ሀፊንግተን ፖስት የተሰኘው ድረ ገፅም እነዚህ 7 ጉዳዮች ፌስቡክ ምን ያህል በህይወታችን ውስጥ ተፅዕኖውን እያሳረፈ መሆኑን ያሳያልና እርሶም የፌስቡክ አድራሻዎን አብዝተው የሚጎበኙት ከሆነ ቆም ብለው ያስቡበት ብሏል።

1.  እንቅልፍ ያሳጣዎታል

በማህበራዊ ሚዲያዎች ሰፊ ጊዜን ማጥፋት የእንቅልፍ ኡደታችን እንደሚያዛባ ጥናቶች ያሳያሉ።

በእንቅልፍ ማጣት ምክንያትም የፌስቡክ ተጠቃሚዎች በድጋሚ ወደ ገፁ እንደሚገቡ ነው የሚነገረው።

በዚህም ለተዛባ እንቅልፍ እና የጤና እክሎች ይዳረጋሉ ይላል መረጃው።

2.  ለድብርት ይዳርጋል

በ2015 የታተመ አንድ ጥናት ፌስቡክ ላይ አፍጥጦ መዋል ከፍተኛ የቅናት ስሜትን እንደሚፈጥር አረጋግጫለሁ ብሏል።

ይህ የቅናት ስሜትም በጊዜ ሂደት ድብርት ውስጥ የመክተት አቅም አለው ነው የተባለው።

ጥናቱን ያደረጉት ዶክተር ማርጋሬት ዱፊ እንደሚሉት፥ በፌስቡክ ጓደኞቻቸው እንቅስቃሴ እና የኑሮ ሁኔታ የሚቀኑ ተጠቃሚዎች ለድብርት የመጋለጥ እድላቸው ከፍተኛ ሆኖ ተገኝቷል።

3. የስማርት ስልክዎን ባትሪ ይሟጥጣል

የፌስቡክ አንድሮይድ እና አይፎን አፕሊኬሽኖች የባትሪ ቀበኞች መሆናቸው ይነገራል።

ይህንን ችግር ያመነው ፌስቡክ ችግሩን ለመቅረፍ እየሰራ መሆኑን መናገሩ የሚታወስ ነው።

ይህ በእንዲህ እንዳለ በስማርት ስልክዎ የሚገኘውን የፌስቡክ አፕሊኬሽን ማጥፋት የስልክዎን የባትሪ እድሜ በ20 በመቶ ያሳድጋልም ተብሏል።

4.  ትኩረትን ያሳጣል

ጥናቶች እንደሚያሳዩት ፌስቡክ አዘውትረውና ለረጅም ስአት የሚጠቀሙ ሰዎች ለነገሮች ትኩረት የመስጠት አቅማቸው እየቀነሰ ነው።

5.  የፍቅር ግንኙነትን ይሸረሽራል

የማህበራዊ ሚዲያዎች ሰዎችን ከተለያዩ የአለማችን ክፍል ማቀራረባቸው እሙን ነው።

ይሁን እንጂ በተለይም የተጋቡ ሰዎችን ከማቀራረብ ይልቅ በማራራቅ ላይ እንደሚገኝ ነው የስነ ልቦና ባለሙያዎች የሚናገሩት።

ፌስቡክን የሙጥኝ ማለት ለፍቅር አጋርዎ መስጠት የሚገባዎን ጊዜ እና እንክብካቤ ሊቀንስ ስለሚችል ራስዎን ይፈትሹ፤ የባለሙያዎቹ ምክር ነው።

6.  ማህበራዊ ግንኙነትን ያኮስሳል

ከማህበራዊ ሚዲያዎች ጋር ያለን የጠበቀ ቁርኝት ዘመዶቻችን አልያም ወዳጆቻችን በአካል ለመገናኘት እንቅፋት ሲሆን ይታያል።

የፌስቡክ ጓደኞቻችን ስለ እኛ አብዝተው የማይጨነቁ እና ሀዘናችን እና ደስታችን ግድ የማይሰጣቸው ብዙዎች መሆናቸውም ይነገራል።

ይህም የቆየ የማህበራዊ ትስስራችን እየቀነስ እንዲሄድ ያደርጋል።

7.  ጊዜ ይገድላል

ምንም እንኳን ፌስቡክን ለበጎ አላማ በጥንቃቄ የሚጠቀሙበት ቢኖሩም አንዳንዶች እንደ ጊዜ ማሳለፊያም ይመለከቱታል።

እናም እርሶም ፌስቡክን የሚጠቀሙት ቁም ነገር ፈልገው ካልሆነ ዝም ብለው ጊዜዎን አያባክኑ ተብሏል፤ ችግሩ ሌላ መዘዝ አለውና።

ፌስቡክን በአግባቡ ካልተጠቀምንበት ጉዳቶቹ ከዚህም ሊከፋ ይችላል የሚሉም አሉ።

ከላይ ለመጠቃቀስ የሞከርናቸው ነጥቦች ሁሉንም የፌስቡክ ተጠቃሚዎች አይመለከቱም።

መረጃውን ልናጋራ የወደድነውም በፌስቡክ ሱስ ለተጠመዱ ሰዎች ምናልባትም አጠቃቀማቸውን ቢያጤኑት በሚል ነው።

ምንጭ፦ www.huffingtonpost.com/

Add your comment

Your email address will not be published.